ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት

Posted in Know How

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና ባለ ልዩ መብቶችን ለማበረታታት የተለያዩ ማምረቻዎችና መገልገያ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል፡፡ በዚህም መሰረት ብዙዎች ተጠቃሚ ሆነው አገራቸውን ወደ ተሸለ ደረጃ ለማድረስ በኢንቨስትመንቱ መስክ ተሰማርተው ልማቱን በማፋጠን ላይ ይገኛሉ፡፡

ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው?

ልዩ ልዩ ሽልማት ያገኙ ፡- ሀገራቸውን ወክለው በውጭ አገራት ለውድድር ሄደው የሚመለሱ ተወዳዳሪዎች ከተሸከርካሪ በስተቀር ያሉ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ይችላሉ፡፡ (መመሪያ ቁጥር 23/1997 እና 28/1998)

 

በውጪ ሀገራት  ለሚያገለግሉ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች፡-

በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ሚሲዮን ሆነው ያገለገሉ ዲፕሎማቶች አገልግሎቱን ጨርሰው ሲመለሱ አንድ ተሸከርካሪና የግል መገልገያ ዕቃዎች ይፈቀድላቸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አካላት፡- (በደንብ ቁጥር አመ147/28/17 ቀን 03/10/2001)

  ከቀረጥ ነፃ ማስገባት የሚችሉት በ10 ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው

ተሸከርካሪና የግል ዕቃዎችን ካስገቡ ከ5 ዓመት በፊት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ አይችሉም፡፡

የአካል ጉዳት ያለባቸው፡-

እንደ ጉዳታቸው መጠን እየታየ አንድ ተሽከርካሪ ማስገባት ይችላሉ፡፡ ይህም በገደብ የተያዘ ነው፡፡ (በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የወጣው መመሪያ ቁጥር 41/2007)

የእነዚህ ደግሞ፡-

  ከ1600 ሲሲ መብለጥ የለበትም

  ከ10 ዓመት በፊት መሸጥna መለወጥ አይቻልም

የጉዳታቸው መጠን የሚገልፅ በሀኪሞች ቦርድ የተሰጠ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

ልዩ አውቶሞቢል የሚያስመጡ ከሆነ የደመወዝ መጠናቸው የተጣራ አመታዊ ገቢ 40,000 ብር መሆን ይኖርበታል፡፡

አውቶሞቢል የሚያስመጡ ከሆነ የተጣራ አመታዊ ገቢያቸው ቢያንስ 80,000 ብር መሆን አለበት፡፡

ይህም ግብር ሰብሳቢው መ/ቤት በአመት የሚያገኙትን ብር ተጠቅሶ ግብር መክፈላቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ የሚሰጣቸው ከሆነ ብቻ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

ለኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ከኢንቨስትመንቱ ጋር የተያያዘ የካፒታል ዕቃዎችን ማስገባት ይችላሉ፡፡ (በደንብ ቁጥር 04/76/32/22 ቀን መጋቢት 02/1996)፣ በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በተሰጠው የተሽከርካሪ ከቀረጥና ታክስ ነፃ የማስገባት መብት መሰረት በተፈቀደው መጠን ማስገባት ይችላሉ፡፡ (በመመሪያ ቁጥር 4/2001 መሰረት) እና በተመረጡ የኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለተሰማሩበት ዘርፍ በተፈቀደላቸው የተሸከርካሪ የቀረጥ ነፃ መብት መሰረት በተፈቀደው መጠን ማስገባት ይችላሉ፡፡ (በመመሪያ ቁጥር 4/2005 መሰረት)

ማንኛውም ለኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ከ5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያላነሰ ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች ኢንቨስት ማድረጋቸው ሲረጋገጥ ተሽከርካሪን የማይጨምር የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች ያስገባሉ፡፡ ይህም ከ10,000 የአሜሪካ ዶላር የማይበልጥ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ጨምሮ አንድ ጊዜ ማስገባት ይችላሉ፡፡ (በደንብ ቁጥር 1.6/5/1 ቀን ሚያዝያ/2001)

በኢትዮጵያ ለመኖር ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡ ቱሪስቶች እና እውነተኛ ጎብኚዎች በጉምሩክ ታሪፍ (ለ) ቁጥር (2) በተመለከተው መሰረት ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር እንዲያስገቡ ሲፈቀድላቸው፤ ይህም የግልና የቤት ውስጥ ዕቃዎች ጠቅላላ ዋጋ ከ5,000 የአሜሪካ ዶላር ያልበለጠ ከሆነ ነው፡፡ (በደንብ ቁጥር 1.6/19/2 ህዳር 9/2002)

በተለያየ አለም አቀፋዊና አህጉር አቀፍ ስራዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር የሚመጡ ወይም በአለም አቀፋዊ ተራድኦ ስምምነት መሰረት የሚመጡ ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት ይፈቀድላቸዋል፡፡

የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች /ሆቴሎች/፣ ለሆቴሎች የካፒታል ዕቃዎች አገልግሎት የሚውሉ አላቂ ዕቃዎች ጨምሮ ማስገባት ይችላሉ፡፡ (የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 5/2007)

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የጅቡቲ ቅ/ፅ/ቤት ሰራተኞች፡-

ሶስት እና ከዚያ በላይ አመታት በጅቡቲ ቅ/ፅ/ቤት የቆየ ሰራተኛ ስራውን/ዋን አጠናቆ/ቃ ሲመለስ/ስትመለስ አንድ አውቶሞቢል እና የግል መገልገያ እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ይፈቀድላዋል፡፡ (በደንብ ቁጥር ተ/ከ/ቀ/ዳ/539 ቀን ጥር 12/2007)

እነዚህ ባለመብቶች፡-

በ10 ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ መኪና የሚያስገቡ ይሆናል፡፡

  መኪናውንም ሆነ ዕቃውን ከቀረጥ ነፃ ካስገቡ ከ5 ዓመት በፊት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ አይችሉም፡፡

 

ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት መፈቀዱ ምን አይነት ጥቅም አለው?

ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱን እና የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል፤

በርካታ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ገብተው መዋለንዋያቸውን ለኢንቨስትመንት እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤

ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድልን ይፈጥራል፣ ከሚሰበሰበው ግብር ልማቶች ይገነባሉ ህብረተሰቡን ከዚህ ተጠቃሚ ይሆናል፤

የቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ሽግግርን ይፈጥራል፤

ይህም በመሆኑ መንግስት በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 11 ቢሊዮን ብር ያህል ከቀረጥ ነፃ መብት በመፍቀዱ ለኢንቨስትመንት መስክ ከፍተኛ ማበረታቻና የመደገፍ ስራ ተሰርቷል፤ በሃገሪቱም ላይ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ተሰርተው በርካታ ባለሀብቶችን መፍጠር ተችሏል፤ ለበርካታ ዜጎችም የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

በትግስት ሙሉጌታ

Visitors: Yesterday 1 | This week 31 | This month 537 | Total 430124

We have 338 guests and no members online