በውጭ አገር የተከፈለ የንግድ ስራ ገቢ እንዴት ይካካሳል?

Posted in Know How

በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው በውጭ አገር ካገኘው የንግድ ስራ ገቢ ላይ የውጭ አገር ግብር ከከፈለ በውጭ አገር የከፈለው የንግድ ስራ ገቢ ግብር እንዲካካስለት ይደረጋል፡፡ የሚካካሰው የግብር መጠንም ፡-

በውጭ አገር ከተከፈለው ገቢ ግብር ፣

በውጭ አገር በተገኘው ገቢ ላይ ሊከፈል ከሚገባው የንግድ ስራ ገቢ ግብር ከሁለቱ ከአነስተኛው የበለጠ አይሆንም፡፡

ከውጭ አገር በተገኘው ገቢ ላይ ሊከፈል የሚገባው የንግድ ስራ ገቢ ግብር የሚሰላው በግብር ከፋዩ ላይ ተፈጻሚ የሚሆነውን አማካይ የንግድ ስራ ገቢ ግብር መጣኔ ግብር ከፋዩ ባገኘው የተጣራ የውጭ አገር ገቢ ላይ ተፈጻሚ በማድረግ ነው፡፡

አማካይ የንግድ ሥራ ገቢ ግብር መጣኔ ማለት ማንኛውም የግብር ማካካሻ ከመደረጉ በፊት በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነው ሰው የግብር ዓመቱ ግብር በሚከፈልበት ገቢ ላይ ተግባራዊ የሚሆነው የግብር መጣኔ ነው፡፡

በውጭ አገር የተከፈለ ግብር ሊካካስ የሚችለው፡-

-    ግብር ከፋዩ ሊከፈል የሚገባውን ግብር ገቢው ከተገኘበት የግብር ዓመት ቀጥሎ ባሉት ሁለት የግብር ዓመታት ወይም ደግሞ ባለስልጣኑ በሚፈቅደው ተጨማሪ ጊዜ ውስጥ የከፈለ እንደሆነና

-       ግብር ከፋዩ በውጭ አገር ለከፈለው ግብር ከውጭ አገር የታክስ ባለስልጣን የተሰጠ ደረሰኝ ያለው እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

በውጭ አገር ለተከፈለ ግብር የተፈቀደ ማካካሻ ከሌሎች ማናቸውም የግብር ማካካሻዎች አስቀድሞ ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡

በአንድ የግብር ዓመት ተካክሶ ያላለቀ የውጭ አገር ግብር ወደ ሌሎች የግብር ዓመታት አይሸጋገርም(Loss cary forward or Loss cary back ward አይፈቀድም)፡፡

የተጣራ የውጭ አገር ገቢ ነው የሚባለው በአንድ የግብር ዓመት ውስጥ ግብር ከፋዩ ካገኘው ጠቅላላ የውጭ አገር ገቢ ላይ የውጭ አገር ገቢውን ለማግኘት ሲባል ብቻ የተደረገ ወጪ፤ የውጭ አገር ገቢ ራሱን የቻለ የገቢ ዓይነት ሆኖ የሚመደብ በመሆኑ የውጭ አገር ገቢውን ለማግኘት በወጣው መጠን ተከፋፍሎ የተመደበ ወጪ ከተቀነሰ በኋላ የሚገኘው ገቢ ነው፡፡

የውጭ አገር የንግድ ስራ ኪሳራዎች

   ግብር ከፋዩ የውጭ አገር ገቢን ለማግኘት ያወጣው ወጪ ተቀናሽ የሚደረገው በውጭ አገር ካገኘው ገቢ ላይ ብቻ ነው፡፡

  በግብር ዓመቱ በውጭ አገር ያጋጠመውን ኪሳራ ግብር ከፋዩ በሚቀጥለው የግብር ዓመት ከውጭ አገር ባገኘው ገቢ ላይ በማካካስ በሰንጠረዠ “ሐ”/ በንግድ ስራ ገቢ ሰንጠረጅ መሰረት ተቀናሽ ይደረግለታል፡፡

በሚቀጥለው የግብር ዓመት ተቀናንሶ ያላለቀ ኪሳራ እስከሚቀጥሉት አምስት የግብር ዓመታት ድረስ ሊሸጋገርና ሊቀናነስ ይችላል፡፡ ሆኖም ኪሳራው ከደረሰበት የግብር አመት በኋላ ካሉት አምስት ዓመታት በላይ ኪሳራውን ለማሸጋገር አይቻልም፡፡

ወደሚቀጥሉት የግብር ዓመታት ማሸጋገር የሚቻለው የሁለት ግብር ዓመታት ኪሳራ ብቻ ነው፡፡

በውጭ አገር የደረሰ ኪሳራ የሚባለው በሰንጠረዥ “ሐ” መሰረት ግብር የሚከፈልበት የውጭ አገር ገቢ ለማግኘት ግብር ከፋዩ ያወጣቸው ወጪዎች መጠን ከጠቅላላው የውጭ አገር ገቢ በልጦ ሲገኝ ነው፡፡

 

ለኩባንያ ካፒታል የሚወሰድ ብድር (Thin capitalization)

በውጭ አገር ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር ያለ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ኩባንያ የግብር ዓመቱ አማካይ ዕዳ ከአማካይ የካፒታል መዋጮው ጋር ሲነጻጸር ከ2ለ1 ሬሽዮ የበለጠ እንደሆነ ኩባንያው ከዚህ ሬሽዮ በላይ በሆነው ዕዳ የከፈለው ወለድ አይቀነስለትም፡፡ ተቀናሽ የማይደረገው የወለድ መጠን ቀጥሎ በተመለከተው ስሌት መሰረት ይወሰናል፡-

በዚህ ስሌት ፡-

)   ኩባንያው በግብር ዓመቱ ተቀናሽ እንዲደረግለት የሚጠይቀው የወለድ ወጪ፤

)   ኩባንያው ከተፈቀደው መጠን በላይ የወሰደው ብድር፤

)  ኩባንያው በግብር ዓመቱ ያለበት አማካይ ዕዳ ነው፡፡

የካፒታል መዋጮ ማለት በውጭ አገር ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር ያለን በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ኩባንያ በሚመለከት የወለድ ክፍያን የማይጨምር ዕዳን መልሶ የመክፈልን ግዴታ የሚያስከትል ብድርን ጨምሮ በሂሳብ ሪፖርት ደረጃዎች መሠረት በግብር ዓመቱ ውስጥ በማናቸውም ጊዜ ተመዝግቦ የሚገኝ ከፍተኛው የኩባንያው የካፒታል መዋጮ ነው፡፡

”አማካይ የካፒታል መዋጮ" ማለት በውጭ አገር ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር የሚገኝን በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ኩባንያ በሚመለከት በግብር ዓመቱ ውስጥ የተከፈለ በሚከተለው ቀመር ስሌቱ የሚከናወን የካፒታል መዋጮ ነው፡፡ 

ለዚህ ስሌት አፈፃፀም፡-

ሀ-በሚቀጥለው የግብር ዓመት ውስጥ በእያንዳንዱ ወር መጨረሻ ለኩባንያው

የተደረገ ጠቅላላ የካፒታል መዋጮ መጠን ነው፡፡

ዕዳ በውጭ አገር ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር የሚገኝን በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ኩባንያ በሚመለከት፣ በፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች በሚወሰነው መሠረት ወለድ የሚከፈልበት የኩባንያው ዕዳ የመክፈል ግዴታ ነው፡፡

አማካይ ዕዳ በውጭ አገር ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር የሚገኝን በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ኩባንያበሚመለከት በግብር ዓመቱ ውስጥ የወሰደው በሚከተለው ቀመር ስሌቱ የሚከናወን ዕዳ ነው፡፡

/12

ለዚህ ስሌት አፈፃፀም፡-

ሀ - በሚቀጥለው የግብር ዓመት ውስጥ በእያንዳንዱ ወር መጨረሻ ኩባንያው የሚፈለግበት ጠቅላላ የዕዳ መጠን ነው፡፡

ዕዳ የመክፈል ግዴታ ከቃል ኪዳን ሰነድ፣ ከሀዋላ እና ከቦንድ የሚመጣን ግዴታ ጨምሮ ለሌላ ሰው ገንዘብ መልሶ የመክፈል ግዴታ ሲሆን፡፡ የሚከተሉትን ግን አይጨምርም ፡-

-  ተከፋይ ሂሳቦችን ወይም

ወለድ የመክፈል ግዴታን የማያስከትል ማናቸውንም ገንዘብ መልሶ የመክፈል ግዴታን፤

በብልጫ የታየ ዕዳ በውጭ አገር ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር ያለን በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ኩባንያ በሚመለከት በግብር ዓመቱ ውስጥ ኩባንያው ያለበት አማካይ ዕዳ በ2ለ1 ቀመር መሠረት ከተፈቀደለት ከፍተኛው አማካይ ዕዳ በላይ የሆነው የገንዘብ መጠን ነው፡፡

ሆኖም በውጭ ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር ያለው በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ  ኩባንያ አማካይ ዕዳ እና አማካይ የካፒታል መዋጮ ከ2ለ1 ሬሽዮ ቢበልጥም የኩባንያው የግብር ዓመቱ አማካይ ዕዳ ግንኙነት ከሌላቸው ሰዎች ከተወሰደው ዕዳ የማይበልጥ ከሆነ ከላይ የተመለከተው ገደብ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

ከላይ የተጠቀሱት በኢትዮጵያ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ባለው የኢትዮጵያ ነዋሪ ባልሆነ ሰው ላይም ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት በሚሆንበት ጊዜ፡-

  ድርጅቱ በውጭ አገር ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር እንዳለ ኩባንያ ሆኖ ይቆጠራል፡፡

የድርጅት አማካይ ዕዳና አማካይ የካፒታል መዋጮ የሚሰላው፡‑

በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ኩባንያ በቋሚነት ለሚሰራ ድርጅት ለማዋል የወሰደው ብድር፣ እና

በኢትዮጰያ ነዋሪ ያልሆነው ኩባንያ በቋሚነት ለሚሰራው ድርጅት መንቀሳቀሻ የመደበው ወይም ያዋለው የካፒታል መዋጮ ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው፡፡

ግንኙነት ከሌላቸው ሰዎች የተወሰደ ዕዳ ማለት በውጭ አገር ባለአክሲዮኖች ቁጥጥር ስር የሚገኘውን ኢትዮጰያዊ ኩባንያ በሚመለከት አንድ የፋይናንሰ ተቋም ኩባንያው የሚገኝበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ግንኙነት በሌላቸው ሰዎች መካከል በሚደረግ ግብይት ዓይነት ሊያበድረው የሚችል ገንዘብ ነው፡፡

 

ግብርን በሚመለከት የሚደረጉ ስምምነቶች (tax treaties)

የግብር ስምምነት ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረትና ታክስ ላለመክፈል የሚደረግን የግብር ስወራ (Tax Evasion) ለመከላከል የሚደረግ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው፡፡ ግብርን የሚመለከቱ ስምምነቶች ከውጭ አገር መንግስት ወይም መንግስታት ጋር የሚደረጉት በገ/ኢ/ት/ሚ/ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጻሚነት ባለው የግብር ስምምነት የውል ቃላትና በዚህ አዋጅ መካከል አለመጣጣም የተፈጠረ እንደሆነ የስምምነቱ ድንጋጌ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

አለመጣጣሙ የተፈጠረው በተዋዋይ አገር ነዋሪ ያልሆነ ሰው ከ50% በላይ ባለቤት የሆነበት ድርጅት የታክስ ነጻ መብትን በሚያሰጥና የግብር ማስከፈያ መጣኔ ቅነሳን በሚያስከትል የግብር ስምምነት ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል  እና

  ከግብር ለመሸሽ የሚደረግን ጥረት ስለመከላከል ከተቀመጡት የአዋጁ ድንጋጌዎች ጋር ከሆነ የስምምነቱ ድንጋጌ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

ተዋዋይ አገር ነዋሪ ባልሆነና ከ50% በላይ የአክሲዮን ባለቤትነት ባለው ሰው ቁጥጥር ስር ያለ በድርጅት ቢሆንም የሚከተሉት ሁኔታዎች ከተሟሉ በታክስ ስምምነቱ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡

የተዋዋይ አገር ነዋሪ ባልሆነ ሰው ከ50% በላይ በባለቤትነት የተያዘው ድርጅት በተዋዋዩ አገር የአክሲዮን ገበያ ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ኩባንያ ከሆነ ወይም፣

በተዋዋዩ አገር በሚገባ የሚንቀሳቀስ የንግድ ስራ ላይ የተሰማራ እንደሆነና በኢትዮጵያ ለተገኘው ገቢ ምንጭ የሆነው ይኸው የንግድ ስራ የሆነ እንደሆነ፡፡

በሚገባ የሚንቀሳቀስ የንግድ ስራ የሚለው ቃል ኩባንያው የገንዘብ ተቋም ወይም የኢንሹራንስ ኩባንያ ካልሆነ በስተቀር የአክሲዮን፣ የዋስትና ሰነዶች ወይም የሌሎች ኢንቨስትመንቶች ባለቤት መሆንን ወይም ማስተዳደርን አይጨምርም፡፡

 

Visitors: Yesterday 51 | This week 69 | This month 365 | Total 431219

We have 248 guests and no members online