የህግ ተገዢነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው

Posted in Latest News

በገቢዎች ሚኒስቴር የህግ ማስበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ዛሬ ጥቅምት 30/2011ዓ.ም ለግልና ለመንግስት ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት በሩብ ዓመቱ ለተፈጠረው የገቢ ጉድለት የህግ ተገዢነት የታክስ አስተዳደሩን የሚፈትን ደረጃ ላይ መድረሱ ዋነኛው ነው ብለዋል እንደ ማሳያ የገለጹት የንግድ ስራ ግብራቸውን ካሳወቁ 2915 ግብር ከፋዮች ውስጥ 67 በመቶ የሚሆኑት ኪሳራ፣ ተመላሽና ባዶ ያሳወቁ ናቸው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ካሳወቁ ግብር ከፋዮች ውስጥ ኪሳራ፣ ባዶና ተመላሽ የጠየቁት 63.9 በመቶ ያህሉ ናቸው፡፡

በህገወጥ ደረሰኝ ወጪን ማናር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ በባዶና በኪሳራ ማሳወቅ እና የሀሰተኛ ደረሰኝ ግብይት በሚኒስቴሩ በተደረገ ጥናት የተለዩ ችግሮች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ያለ ምንም የእቃ ወይም የአገልግሎት ልውውጥ ደረሰኝ ብቻ በመሸጥ ተግባር የተሰማሩ 124 ድርጅቶችን ዝርዝር በህገወጥ ደረሰኝ አቅራቢነት መያዙን አስታውቀዋል፡፡

የድርጅቶቹን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረጉት ሚኒስትሩ እነዚህ ድርጅቶች ሐሰተኛ ማንነት ይዘው የተቋቋሙ በሐሰተኛ መታወቂያ፣ንግድ ፈቃድ፣የመተዳደሪያ ደንብ እና አድራሻ ተመዝግበው የሚሰሩ ናቸው፤ እነዚህ ሐሰተኛ ድርጅቶች ከግብር ከፋይ ጋር ባደረጉት ግብይት አራት ቢሊየን ብር የኦዲት ግኝት መኖሩን ተናግረው መስሪያቤቱ ድርጅቶቹን የመለየትና ለህዝብ ይፋ ማድረጉን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ግብር ከፋዩ ግብይት ሲያከናውን ህጋዊ ምዝገባ፣ አድራሻ፣ ትክክለኛ ሰነድ፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ጋር  በማገናዘብ መሆን አለበት ያሉት አቶ ዘመዴ ህገወጥ ደረሰኞች በኦዲት የሚገኙ በመሆኑ ግብር ከፋዩ ከመጠቀም እንዲቆጠብ በስህተት ደረሰኞችን ገብይቶም ከሆነ ለግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ማቅረብ እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

#በራሄልወልዴ

 

Visitors: Yesterday 43 | This week 88 | This month 779 | Total 434506

We have 137 guests and no members online