የፋይናንስ ግልጸኝነት

የአንድን ተቋም የስራ እንቅስቃሴ ከማሳወቅ ባለፈ ያከናወናቸውን ተግባራት የሚፈጽምበትን በጀት ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ማድረግ በሰለጠኑት ሀገራት የተለመደ ነው፡፡ አንድ ተቋም ለሚሰራው ሥራ ከህብረተሰቡ በግብር መልክ የተሰበሰበው በጀት የሚመደብለት እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ገንዘቡ በትክክለኛ መንገድ እና ለታለመለት ተግባር ስለመዋሉ ለመቆጣጠር እንዲሁም ተጠያቂነት እንዲኖር ስለሚያስችል የበጀት አፈጻጸም፣ የኦዲት ግኝትን፣ የስራ አፈጻጸም እና መሰል መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ይገባል፡፡

በዚህም መሰረት የገቢዎች ሚኒስቴር በየጊዜው መሰል መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ የቆየ ሲሆን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የስድሰት ወራት የበጀት አጠቃቀም እና የፕሮጀክቶች አፈፃፀም አቅርበናል፡፡

የበጀት አጠቃቀም እና የፕሮጀክቶች አፈፃፀም

  • ሀገር ውስጥ ታክስ

በበጀት አጠቃቀምና አያያዝ ጋር ግልፀኝነት መፍጠር አስፈላጊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቅርንጫፍ /ቤቶችና ዋናው መስሪያ ቤት ውስጥ ያሉ የስራ ክፍሎች የተመደበላቸውን 2013 በጀት እንዲያውቁ ከማድረግና አጠቃቀሙን ከመከታተል ጎን ለጎን 2012 በጀት አጠቃቀም ሂሳብ የመዝጋት ስራ ተከናውኗል። 2013 በጀት አጠቃቀምን በተመለከተ በስድስት ወራት ለመደበኛ እና ለካፒታል የተመደበውን በጀት ባለበጀቱ በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን የመከታተል፣ የመደገፍና የአጠቃቀም መረጃ የመያዝ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለመደበኛ (ለደመወዝና ሥራ ማስኬጃ) የተስተካከለ በጀት ብር 1,792,562,340.00 እና የካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ብር 587,000,000.00 በድምሩ ብር 2,379,562,340.00 ተስተካክሎ ተመድቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት ለደመወዝና ሥራ ማስኬጃ ለመጠቀም ከታቀደው ብር 969,865,299.44 ውስጥ ብር 853,417,064.67 ወይም 87.99 በመቶ ወጪ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል የካፒታል በጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ብር 220,376,573.27 ለመጠቀም ታቅዶ ብር 101,807,208.39 (46.20 በመቶ) ወጪ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ለመደበኛ እና ለካፒታል ብር 1,190,241,872.71 ወጪ ለማድረግ ታቅዶ ብር 955,224,273.06 ወጪ ሲሆን አፈፃፀሙም 80.25 በመቶ ነው፡፡

ለካፒታል ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ማነስ ተጠቃሽ ምክንያቶች: -

ለአንድ መስኮት አገልግሎት የሚውል የቋሚ ዕቃ ግዥ የብር 54,896,384.14 ኤልሲ ሲከፈት ከበጀት የተቀነሰ ቢሆንም እቃ እስከሚገባ ድረስ በተከፋይ የተያዘ በመሆኑ፣

ለመቀሌ //ቤት የቢሮ ግንባታ ቅድመ ክፍያ 10 በመቶ ብር 28,055,904.31 የተከፈለ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት የክፍያ ሰርተፍኬት ሲያቀርብ ተቀናሽ የሚሆን በመሆኑ በድምሩ ብር 82,952, 288.45 በተከፋይ ተይዞ ወደ ወጪ ዓርስት በሲስተም ባለመመዝገቡ የተነሳ ነው። ከዚህ ውጪ የክንትስራክሽን ፕሮጀክቶች ያለፉት ስድስት ወራት አፈፃፀም ለብቻው ተነጥሎ ሲታይ የብር 68,447,310.52 በስራ ላይ ያዋለ ሲሆን አፈፃፀሙም 95.06 በመቶ ሊሆን ችሏል።

በተቋም ጋራዥ 237 በካምፓኒ 10 በግል ጋራዥ 11 ተሸከርካሪዎች የተጠገኑ ሲሆን እንዲሁም በግጭት ምክንያት 6 ተሸከርካሪዎች የኢንሹራንስ ሽፋን አግኝተው ተጠግነው የወጡ ሲሆን በድምሩ 264 ተሸከርካሪዎች ተጠግነው ወጥተዋል፡፡ በውስጥ ጋራዥ አገልግሎት በኩል 631ሺህ 800 ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ማዳን ተችሏል።

ከተለያዩ ስራ ክፍሎችና በህንፃእናእድሳት ምክንያት የተሰበሰቡ ተወጋጅ ንብረቶችን በማደራጀት የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት እንዲረከብ በማድረግ ከሽያጭ ብር 767,514 ገቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

  • ጉምሩክ

በበጀት ዓመቱ ለመደበኛ (ለደመወዝና ሥራ ማስኬጃ) ብር 2,281,314,310.00 እና ለካፒታል ፕሮጀክቶች ብር 413,000,000 በድምሩ ብር 2,694,314,310.00 ተስተካክሎ የተመደበው በጀት ለሁሉም //ቤቶች ተደልድሎ ተልኮላቸዋል። በግማሽ ዓመቱ ለደመወዝና ሥራ ማስኬጃ ለመጠቀም ከታቀደው ብር 1,488,042,976.78 ውስጥ ብር 1,092,368,587.12 ወይም 73.41 በመቶ ወጪ ተደርጓል፡፡ የካፒታል በጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ለበጀት ዓመቱ ተስተካክሎ የተፈቀደ ብር 413 ሚሊዮን ሲሆን በግማሽ ዓመቱ ብር 123.68 ሚሊዮን ለመጠቀም ታቅዶ ብር 28.93 (23.39 በመቶ) ሚሊዮን ወጪ ተደርጓል፡፡