faq

በገቢዎች ሚኒስቴር በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸዉ

 

Q1.አስመጪዎች እና ላኪዎች የጉምሩክ ስነስርዓት ለማስፈፀም ለጉምሩክ ማቅረብ የሚገባቸው መረጃዎች (ሰነዶች) ምን ምን ናቸው?

መልስ. በፅሁፍ ወይም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የእቃ ዲክላራሲዮን ለጉምሩክ ሲቀርብ መሟላት ያለባቸዉ ሰነዶች የታደሰ የንግድ ፍቃድ፣ የማጓጓዣ፣ የዋጋና የዕቃ ዝርዝር መግለጫ የያዙ ሰነዶች፣ የባንክ ፍቃድ፣ የስሪት ሀገር ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እና በመመሪያ የሚወሰኑ ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶች ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡

Q2.አስቀድሞ ቀረጥ እና ታክስ የተከፈለባቸው ነገር ግን ከፊሉ ዕቃ የጎደለ በሚሆንበት ጊዜ የተከፈለ ቀረጥ የሚመለስበት ሁኔታ አለ?

መልስ.በጎደለው ዕቃ ላይ የተከፈለው ቀረጥ እና ታክስ ተመላሽ ይደረጋል፡፡ አለበለዚያም ሳይመጣ የቀረው ዕቃ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል፡፡

Q3.ከውጭ አገር ጠቅልሎ ወደ ሐገሩ የሚመለስ ሰው የግል መገልገያ ዕቃዎችን ይዞ መግባት ይችላል ወይ?

መልስ.አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ውጭ ሀገር ቆይቶ ጠቅልሎ የሚመለስ ተመላሽ ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጲያዊ የግል መገልገያ እቃዎችን ከቀረጥ እና ታከስ ነጻ ማስገባት የሚችል ሲሆን፣ ነገር ግን ተሸከርካሪ አውቶሞቢል ለማስገባት 5 ዓመትና ከዛ በላይ ውጭ ሀገር መቆየት እና አስፈላጊውን ቀረጥና ታክስ መክፈል ይኖርበታል፡፡

Q4.ከቀረጥ ነጻ የገባ ተሽከርካሪ የቀረጥ ነጻ መብት ለሌለው ሰው መሸጥ ይቻላል?

መልስ.አዎ፡፡ በተሸከርካሪው ላይ የሚፈለገውን ቀሪ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ በመክፈል መሸጥ ይቻላል፡፡

Q5.እቃዎችን ያለ አስመጪነት ንግድ ፍቃድ ለአንድ ግዜ ብቻ ማምጣት ይቻላል?

መልስ.ለመንገደኞችና ለተመላሾች በህግ በተቀመጠው መሰረት ካልሆነ በስተቀር ያለንግድ ፍቃድ እቃዎችን ወደ ሀገር ወስጥ ማስገባት አይቻልም፡፡

Q6.ወደ ሀገር የሚገቡ ዕቃዎች ቀረጥና ታክስ የሚወሰነው እንዴት ነው?

መልስ.የዕቃዎች ቀረጥና ታክስ የሚወሰነው በዕቃው አጠቃላይ የCIF ዋጋ ማለትም የመግዣ ዋጋ፣ የማጓጓዣ ዋጋ፣ ኢንሹራንስና ሌሎች ወጪዎች ድምር በመውሰድ እና የዕቃውን የታሪፍ ምጣኔ መሰረትበማድረግ ነው፡፡

Q7.የዕቃዎችን የቀረጥና ታክስ ምጣኔ እንዴት ማወቅ እችላለሁ?

መልስ.የዕቃዎች የቀረጥና ታክስ ምጣኔ ወይም የታሪፍ ልክ በታሪፍ መጽሀፍ ላይ የዕቃዎችን የታሪፍ ቁጥር (HS Code) መሰረት በማድግ የተቀመጠ ሲሆን፣ በተጨማሪም በጉምሩክ ትሬድ ፖርታል ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ ትሬድ ፖርታሉን በመጠቀም የዕቃዎችን የታሪፍ መጠን በቀላሉ ማስላት (calculate) ማድረግ ይቻላል፡፡

Q8.የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዴት ማግኝት እንችላለን?

መልስ.የአንድ መስኮት (single window) አገልግሎት ለማግኘት ኢንተርኔት ላይ (Ethiopian single window) በሚል በመፈለግ ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ አጠቃቀሙን ከተጫኑት ቪዲዮዎች መመልከት ይቻላል፡፡

Q9.ባንኮች በዋስትና የያዙትን ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕቃዎች በጨረታ መሸጥ ይችላሉ?

መልስ.ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሽያጩ የተከናወነው የቀረጥ ነፃ መብት ላላቸው ከሆነ፣ ቀረጡ የማይከፈል ሲሆን፣ መብቱ ለሌላቸው ከተሸጠ ሊሰበሰብ የሚገባው የጉምሩክ ቀረጥ እና ሌሎች ታክሶች ለጉምሩክ ገቢ መደረግ ይኖርበታል፡፡

Q10.ለኮንስትራክሽ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችና ማሽነሪዎች ከውጭ ሲገቡ ቀረጥና ታክስ ይከፈልባቸዋል?

መልስ.ለኢንቨስትመንት አገልግሎትም ሆነ ለንግድ የሚውሉ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችና ማሽነሪዎች ከውጭ ሲገቡ ቀረጥና ታክስ አይከፈልባቸውም፡፡

Q11.በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማራ የውጭ ሀገር ባለሀብት የካፒታል ዕቃዎችን ያለ ውጭ ምንዛሪ ክፍያ ወደ አገር ማስገባት ይችላል ወይ?

መልስ.በኢንቨስትመንት የስራ መስክ ላይ የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች የካፒታል ዕቃዎችን ያለውጭ ምንዛሪ (በፍራንኮ ቫሉታ) ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ይችላሉ፡፡

Q12.ለንግድ ማስተዋወቅና ለናሙና እንዲውሉ ዕቃዎችን ያለውጭ ምንዛሬ ፈቃድ (ፍራንኮ ቫሉታ) ወደ አገር ማስገባት ይቻላል ወይ?

መልስ.ከስራቸው ጋር ተያያዥነት ያለው የንግድ ስራ ፈቃድ እስካቀረቡ ድረስ ለሳምፕል (ናሙና) ዋጋቸው እስከ 5000 ዶላር፣ ለማስተዋወቅ (የምርቱን አርማ፤የድርጅቱን ስም፤ልዩ መለያ ወይም ምልክት አገልግሎት) የንግድ መጠን የሌላቸው እስከ 4000 ዶላር ድረስ ዕቃዎች ቀረጥ በመክፈል ማስገባት ይቻላል፡፡

Q13.ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር እንዳይገቡ የተደረገ ገደብ አለ ወይ?

መልስ.ተገቢው የጉምሩክ ቀረጥ እና ታክስ እስከተከፈለ ድረስ ያገለገሉ ተሸከርካሪዎች ማስገባት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እንደየምርት ዘመናቸው የታከስ ምጣኔው የሚለያይ ሲሆን፣ አሮጌ ተሸክርካሪዎች ከፍተኛ ቀረጥ እና ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡

Q14.በዋስትና ዕቃዎችን በጊዜያዊነት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት የሚቻለው በምን በምን ሁኔታዎች ነው?

መልስ.ዕቃዎች በጊዜያዊነት ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ የሚችሉት በቱሪዝም እና ባሕል ልውውጥ፤ ንግድን ለማስተዋወቅ፤ ለግንባታ ስራ፤ ለምክር አገልግሎት፤ ከእርዳታ ስራ ጋር በተያያዘ ወይም በፕሮጀክት ስምምነት መሰረት ሲሆን፣ የሚያዘው የዋስትና ዓይነት፣ ዲፖዚት፣ የኢንሹራንስ ቦንድ፣ የባንክ ጋራንቲ ወይም የጹሁፍ ደብዳቤ ሊሆን ይችላል፡፡

Q15.በስጦታ የሚመጡ ዕቃዎች ቀረጥ ይከፈልባቸዋል ወይ? ተቀባይ ምን ምን ማስረጃ መቅረብ ይኖርበታል?

መልስ.ዕቃ በስጦታ የመጣለት ሰው የመጣለትን ዕቃ የዕቃ ዝርዝር መግለጫ፣ የተላከውን ዕቃ ዋጋ ሰነድ፣ የመኖሪያ መታወቂያና የላከለትን ሰው ማንነት የሚገልጽ ማስረጃ በማቅረብ ቀረጥና ታክስ ከፍሎ መረከብ ይችላል፡፡

Q16.የተሸከርካሪዎችን የታሪፍ እና የቀረጥ መጠን ለማወቅ እንዴት እንችላለን?

መልስ.የተሸከርካሪዎችን የታሪፍ ምጣኔ ለማወቅ የታሪፍ መፅሐፉን መመልከት ነው፡፡ የተሸከርካሪዎችን የቀረጥ መጠን ለመወሰን የተሽከርካሪው ትክክለኛ የገበያ ዋጋ፣ ሲሲ እና የምርት ዘመኑ መገለጽ አለበት፡፡

Q17.ከቀረጥ ነፃ የገቡ የካፒታል ዕቃዎች በሽያጭ ለሌላ ሰው ሊዛወሩ ይችላሉ?

መልስ.የቀረጥ ነፃ መብት ያለው ሰው የካፒታል ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ካስገባ በኋላ ለሌላ በነዚሁ አይነት ዕቃዎች ለመጠቀም የሚያስችል የቀረጥ ነፃ መብት ላለው ሰው ከቀረጥ ነፃ መሸጥ/ማዛወር ይቻላል፡፡ መብቱ ለሌለው ሰው የሚዛወር ከሆነ ግን በዕቃው ላይ የሚፈለገው ቀረጥና ታክስ ሊከፈል ይገባል፡፡

Q18.በጊዜያዊነት ወደ ሀገር ያስገባናቸውን ማሽኖች ሀገር ውስጥ የገቡበትን ዓላማ እንዳጠናቀቁ ለማስወጣት ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

መልስ.በጊዜያዊነት የገቡ እቃዎች የገቡበትን ዓላማ እንደጨረሱ ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ እስከሚወጡበት ጊዜ በሚታሰበው የዕርጅና ቅናሽ ላይ አስፈላጊውን ቀረጥ እና ታክስ ከፍለው በገቡበት ሁኔታ ተመልሰው ሊወጡ ይገባል፡፡

Q19.አስቀድሞ ቀረጥ እና ታክስ የተከፈለባቸው ነገር ግን ከፊሉ ዕቃ የጎደለና ወደ ሀገር ውስጥ ያልገባ በሚሆንበት ጊዜ የተከፈለው ቀረጥ የሚመለስበት ሁኔታ አለ?

መልስ.በጎደለው ዕቃ ላይ የተከፈለው ቀረጥ እና ታክስ ተመላሽ ይደረጋል፡፡ አለበለዚያም ሳይመጣ የቀረው ዕቃ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል፡፡

Q20. በንግድ ስራ ዘርፍ ለመሰማራት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) ለማውጣት በታክስ ከፋዩ ዝገብ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምን ምን ናቸው?

መልስ.አንድ ሰው በታክስ ከፋይነት ለመመዝገብ የንግድ ስራውን የሚሰራው ተከራይቶ ከሆነ የቤት ኪራይ ውሉን በመያዝ በአካባቢዎ ወደሚገኝ ገቢዎች ቅ/ጽ/ቤት በመሄድ በባለስልጣኑ የተዘጋጀውን ቅፅ ሞልቶ ማቅረብና የማንነት አካላዊ መረጃ መስጠት፣ ወቅታዊ ወይም የታደሰ የነዋሪነት መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ወይም የመንጃ ፈቃድ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

Q21.ታክስ በምናሳውቅበት ጊዜ የሂሳብ ስሌት ስህተት አጋጥሞን ነበር በምን መልኩ ማስተካከል እንችላለን?

መልስ.ታክስ ከፋዩ የራስ ታክስ ስሌት እንዲሻሻል ለታክስ ባለስልጣኑ ማመልከቻ ማቅረብ የሚኖርበት ሲሆን፣ ማሻሻል የሚችለውም የመጀመሪያ የራስ ታክስ ስሌት ማስታወቂያ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ሆኖ ለደረጃ ሀ ግብር ከፋይ ባሉት አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ፣ ለደረጃ ለ እና ሐ ግብር ከፋይ ባሉት ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

Q22. የካፒታል ሀብቶችን በማስተላለፍ የሚገኝ ጥቅም ላይ ግብር መክፈል ያለበት ማነው?

የካፒታል ሀብቶችን በማስተላለፍ የሚገኝ ጥቅም ላይ ግብር መክፈል ያለበት ጥቅም ያገኘው ሰው ነው::

Q23.ብድርን በተመለከተ ግብር ከፋዩ ለስራው ማካሄጃ ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ሲበደር ማሟላት ያለበት ማስረጃዎች ምን ምን ናቸው?

ግብር ከፋዩ በቅድሚያ የእዳ መመዝገቢያ መዝገብ መያዝ አለበት፣ በብድር ያገኘው ገንዘብ ገቢ ለማግኘት ለንግድ ስራው ዋስትና ለመስጠትና የንግድ ስራውን ለማስቀጠል እንደዋለ የሚያሳይ ሰነድ ሊኖረው ይገባል፣ ሰነዶችን የማረጋገጥና የመመዝገብ ስልጣን በተሰጠው አካል በብድሩ ላይ በሚያስከፍለው የቴምብር ቀረጥ መጠን የተከፈለ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብና የወለድ ወጪን ለመያዝ እንዲያስችለን ተገቢው የወለድ ግብር በሰንጠረዥ “መ” መሰረት ስለመከፈሉ የሚያሳይ ማስረጃ ሊኖረው ይገባል፡፡

Q24. የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽንን በወቅቱ አለማሳደስ የሚያስከትለው ቅጣት ምንድነው?

በአመት አንድ ጊዜ በአገልግሎት ማዕከል የቴክኒክ ምርመራ ያላደረገ ግብር ከፋይ ብር 25 ሺህ ( ሀያ አምስት ሺህ) ቅጣት ይከፍላል፡፡

Q25.ተቀናሽ የሚደረገው ሁለት በመቶ ዊዝሆልዲንግ ታክስ የሚሰላበት የእቃ ወይም የአገልግሎት የክፍያ መጠን የተጨማሪ እሴት ታክሱን ይጨምራል/አይጨምርም?

መልስ.ዊዝሆልዲንግ ታክስ የሚሰላበት የእቃ ወይም የአገልግሎት ጠቅላላ የክፍያ መጠን በአገልግሎቱ ላይ የሚከፈል የተጨማሪ እሴት ታክስን አይጨምርም፡፡

Q26. የብረታ ብረት፣ የአውቶሞቲቭ እና ኢንዱስትሪያል ዘይቶች እና ቅባቶች በአገር ውስጥ ሲሸጡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፈልበታል /አይከፈልበትም?

መልስ.የብረታ ብረት፣ የአውቶሞቲቭ እና ኢንዱስትሪያል ዘይቶች እና ቅባቶች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ ሲሸጡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበሰብባቸዋል፡፡

Q27. አንድ ድርጅት በታክስ እፎይታ ጊዜ ውስጥ እያለ ሁለት በመቶ የቅድመ ግብር ክፍያ ይመለከተዋል /አይመለከተውም?

መልስ.በታክስ እፎይታ ጊዜ ውስጥ ያለ ድርጅት የቅድመ ግብር ክፍያ ሁለት በመቶ አይመለከተውም፡፡

Q28. የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በሀገር ውስጥ ግብይት ሲፈፀምባቸው የተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፈልባቸዋል/ አይከፈልባቸውም?

መልስ.የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ከውጭ ሲገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈፀምባቸው ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ናቸው፡፡

Q29.የህንፃ የእርጅና ቅናሽ ወጭ መሰላት የሚጀመርበት ጊዜ መቼ ነው?

መልስ.የህንፃ ግንባታዎችን የሚቆጣጠረው የሚመለከተው የመንግስት መ/ቤት (ባለስልጣን) ለግብር ከፋዩ የህንፃው ግንባታ መጠናቀቁን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

Q30.በመያዣነት በሚያዝ ገንዘብ ላይ (Retention) የተጨማሪ እሴታ ታክስ ይከፈልበታል/ አይከፈልበትም?

መልስ.በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ መሰረት አገልግሎት በተሰጠበት ጊዜ ግብይት እንደተከናወነ የሚቆጠር በመሆኑ በመያዣነት በሚያዝ ገንዘብ (Retention) ላይ የተጨማሪ እሴታ ታክስ ሊከፈልበት ይገባል፡፡

Q31.ደረሰኝ አሳትመው መጠቀም ከማይገደዱ ሰዎች ላይ ግብይት በሚፈፀምበት ጊዜ ምን አይነት ደረሰኝ መጠቀም እንችላለን?

መልስ.የሂሳብ መዝገብ የሚይዝ ታክስ ከፋይ የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ከሌለባቸው ታክስ ከፋዮች ጋር ለሚያደርገው ግብይት ከታክስ ባለስልጣኑ በማስፈቀድ የወጭ ማስረጃ የግዥ ማረጋገጫ ደረሰኝ (purchase Voucher) አሳትሞ መጠቀም አለበት፡፡

Q32.አንድ ተቀጣሪ ከአንድ በላይ በመቀጠር የሚያገኘው ገቢ ያለው እንደሆነ የግብር አከፋፈሉን በተመለከተ የሚሰላው እንዴት ነው?

መልስ.ቀጣሪው ተቀጣሪው ከአንድ በላይ በመቀጠር የሚያገኘው ገቢ እንዳለው ያወቀና ሌሎቹ ቀጣሪዎች በጠቅላላው የተቀጣሪው ገቢ ላይ የገቢ ግብሩን ቀንሰው እንደማያስቀሩ ያወቀ እንደሆነ ቀጣሪው የተቀጣሪውን ገቢ በማጠቃለል የገቢ ግብር ቀንሶ የማስቀረት ግዴታ አለበት፡፡

Q33.አንድ ሰው ግብር የሚከፈልበትን የማይንቀሳቀስ ሀብት በሚሸጥበት ጊዜ መከፈል ያለበት ታክስ ምንድነው?

መልስ.ግብር የሚከፈልበት ሀብት የተላለፈበት ዋጋ ሀብቱ በተላለፈበት ጊዜ ከነበረው ዋጋ በልጦ የተገኘ ከሆነ በተገኘው ጥቅም ላይ 15 በመቶ ታክስ ይከፈልበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግብይቱ ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበሰብበታል፡፡

Q34.የውሎ አበል ክፍያ እንዲሁም የመዘዋወሪያ አበል ክፍያ ከግብር ነፃ የሚሆነው በምን ያህል መጠን ነው?

መልስ.የውሎ አበል አንድ ሰራተኛ የተቀጠረበትን ስራ ለማከናወን የቀን የውሎ አበል ከግብር ነፃ የሚደረገው ከብር 500 ወይም ከደሞዙ 4% (አራት ፐርሰንት) ከሁለቱ ከፍተኛ ከሆነው መጠን ባልበለጠ ብቻ ሲሆን፤ የመዘዋወሪያ አበልን በተመለከተ ከጠቅላላ የወር ደመወዝ ¼ ወይም ከብር 2200 የማይበልጥ ሲሆን፣ ከግብር ነፃ የሚደረገው የመዘዋወሪያ አበል በማንኛውም ሁኔታ ከብር 2200 መብለጥ አይችልም፡፡

Q35. የሽያጭመመዝገቢያ መሳሪያ /Cash Register Machine/ ተጠቃሚዎች ማሽኑ ብልሽት ሲያጋጥመው መብራት በሚጠፋበት ወቅት እንዲሁም የአድራሻ ለውጥ በሚያደርጉበት ጊዜ ያለው አጠቃላይ መረጃ ቢብራራ?

መልስ. የሽያጭመመዝገቢያ መሳሪያው ብልሽት በሚያጋጥምበት ጊዜ ለአገልግሎት ማዕከሉ እና ለባለስልጣን መ/ቤቱ በ2 ሰዓት ውስጥ ማሳወቅ መብራት በሚጠፋበት ጊዜ ለባላስልጣን መ/ቤቱ ወድያውኑ በስልክ ወይም በአካል ማሳወቅ፣ አድራሻ ለውጥ በሚፈልጉ ጊዜ አድራሻ ለውጥ ያደረጉበትን ንግድ ፈቃድ እና መመልከቻ በማያያዝ ለባለስልጣን መ/ቤቱ ማቅረብ ያለባቸው መሆኑን እንገልፃለን፡፡

Q36.የወጭ መጋራት ክፍያ /cost sharing/ ክሊራንስ በክፍሎች ይሰጣል?

መልስ. ተማሪዎች ለእንግልት እና ለተጨማሪ ወጪ ሳይዳረጉ አገልግሎት ከሰጡበት ተቋም የሚፈለግባቸውን ክፍያ /አገልግሎት/ ስለማጠናቀቃቸው የሚገልፅ ደብዳቤ ሰጽፈው ሲቀርቡ በአካባቢያቸው ከሚገኘው ገቢ ሰብሳቢ ቅ/ጽ/ቤት ክሊራንስ መውሰድ የሚችሉ መሆኑን እንገለፃለን፡፡

Q37. የከፍተኛ ትምህርት የወጪ መጋራት ክፍያ /cost sharing/ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኃላ በምን ያህል ጊዜ ገንዘብ መክፈል እንደሚገባ አገልግሎት ከመስጠት አንፃር እንዲሁም አጠቃላይ ያለው ሁኔታ በዝርዝር ቢገለጽ?

መልስ. የከፍተኛ ትምህርት የወጪ መጋራት ክፍያ /cost sharing/ በተመለከተ ከአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ በኃላ ክፍያው መጀመር ያለበት ሲሆን፤ አገልግሎት ከመስጠት አንፃር በጤናና በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡበትንና አገልግሎት የሰጡበትን ማስረጃ በማቅረብ ወደሚገኘው ገቢ ሰብሳቢ ቅ/ፅ/ቤት በመሄድ መስተናገድ የሚችሉ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡

Q38. ወደ ውጭ ምርቶቻቸውን የሚልኩ ባለሃብቶች በሚልኩበት ጊዜ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ 0% ሆኖ ሳለ ቫት/VAT/ ተመዝጋቢ የመሆናቸው ምክንያት በግልጽ ቢብራራ?

መልስ. ወደ ውጪ ምርቶቻቸውን የሚልኩ ባለሃብቶች የዜሮ ተመን ቫት ተመዝጋቢ የመሆናቸው ምክንያት ለግብዓት የተከፈለውን ታክስ ተማላሽ ለማድረግና የውጭ ንግዱን ከማበረታታት አንፃር ነው፡፡

Q39. ቅጣት ብቻ የተጣለበት ግብር ከፋይ ቅጣት እንዲነሳለት በሚጠይቅበት ጊዜ ስንት መቶኛ ይነሳለታል?

መልስ. አስተዳዳራዊ መቀመጫዎች እንደማይነሱ ከተገለፁት ሁኔታዎች በስተቀር በግብርና ታክስ ላይ የተጣሉ አስተዳደራዊ መቀመጫዎች እንደሁኔታው በሙሉ ወይም በከፊል ሊነሱ ይችላሉ፡፡

Q40. በኢትዮጵያ ነዋሪ ሆኖ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር/TIN/ የሌለው ሰው በሚሰጠው አገልግሎት ክፍያ ላይ ምን ያህል % ነው ግብር የሚከፍለው?

መልስ. ቅድመ ግብር ክፍያ ቀንሰው እንዲስቀሩ ሀላፊነት የተጣለባቸው አካላት አገልግሎቱን ያቀረቡ ሰዎች የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ከሌላቸው 30% (ሰላሳ ፐርሰንት) ቀንሰው ገቢ እንዲያደርጉ በህጉ ተደንግጓል፡፡