የተሽከርካሪ ቀረጥና ታክስ አወሳሰን

 

 

 

የተሽከርካሪ  ቀረጥና  ታክስ  አወሳሰን

ተሽከርካሪ ወደ ሀገር ሲገባ ቀረጥና ታክስ የሚታሰበው ተሽከርካሪው ዓይነት (የቤት አውቶሞቢል፣ የህዝብ ማመላለሻ ወይም የዕቃ ማመላለሻ፣ ልዩ ልዩ) የተሸከርካሪዉን የመጫን አቅም(የሰው ብዛት፣ የጭነት ኪሎ መጠን)፣ ጉልበት (ለቤት አውቶሞቢሎች)  መሰረት በማድረግ  እንዲሁም CIF (የተገዛበት ዋጋ + የትራንስፖርት ወጪ + የኢንሹራንስ ወጪ እና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ) በሚገኘዉ ጠቅላላ ወጪ ነው፡፡  

 

ተገጣጥመው ወደ ሀገር የሚገቡ አዲስ የቤት አውቶሞቢል ተሽከርካሪዎች ጉልበታቸው እስከ 1300 ከሆነ 75.67%ሲሆን ጉልበታቸው ከ1301 እስከ 1800  ደግሞ 116.79% እንዲሁም ከ1800 በላይ ጉልበት ያላቸው ከሆኑ ደግሞ  231.9% አጠቃላይ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ምጣኔ ተጥሎባቸዋል፡፡  ሹፌሩን ጨምሮ እስከ 16 የመቀመጫ አቅም ያላቸው የሰው ማጓጓዣዎች እና እስከ 1.5 ቶን እቃ የመጫን አቅም ያላቸው የእቃ ማጓጓዣዎች  አጠቃላይ የቀረጥና ታክስ ምጣኔ 52.5% ሲሆን ከ16 ሰው በላይ  የሚጭኑ የህዝብ ማመላለሻዎች እና ከ1.5 ቶን በላይ እቃ የሚጭኑ ተሸከራካሪዎች ደግሞ 29.5% አጠቃላይ የቀረጥና ታክስ ምጣኔ ተጥሎባቸዋል፡፡  በሌላ በኩል ሀገር ውስጥ ለመገጣጠም በአምራች ድርጅቶች ወደ ሀገር የሚገቡ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል የተበተኑ (CKD/SKD) የሆኑ ተሽከራካሪዎች በተመለከተ በአዲስ ይዞታ ተገጣጥመው ወደ ሀገር ከሚገቡ ተሸከራካሪዎች በተለየ በዝቅተኛ የቀረጥና ታክስ ምጣኔ የሚስተናገዱ ሲሆን በተቃራኒው  ያገለገሉ(USED) ተሽከራካሪዎች ደግሞ ከፍተኛ የኤክሳይዝ ታክስ ስለተጣለባቸው በአዲስ ይዞታ ከሚገቡ ተሸከራካሪዎች በአንፃራዊነት በጣም ከፍተኛ አጠቃላይ የቀረጥና ታክስ ምጣኔ አላቸው፡፡ 

 

የተሽከርካሪው የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ (duty paying value) በተሽከርካሪው ጠቅላላ ቀረጥና ታክስ ማስከፈያ ምጣኔ ተባዝቶ የብዜቱ ውጤት ተከፋዩ ቀረጥና ታክስ ይሆናል፡፡ እንደ ተሽከርካሪው አይነት ወደ ሀገር የሚገቡ የተሸከርካሪዎች ላይ እስከ አራት ዓይነት የቀረጥና ታክስ ዓይነት የሚጣልባቸው ሲሆን ከአምራች ድርጅቶች ውጪ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች   ከሆኑ ደግሞ በተጨማሪነት የዊዝሆልዲንግ ታክስ ይሰበሰባል፡፡ የቀረጥና ታክስ ማስከፈያ መሠረት(Tax base) የሚሆነው የእቃው ዋጋ(CIF) እና  በቅድም ተከተል የሚሰላው የቀረጥ ወይም ታክስ መጠን (የጉምሩክ ቀረጥ፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ የተጨማሪ ዕሴት ታክስ፣ ሱር ታክስ) ድምር ይሆናል፡፡

 

የቀረጥና ታክስ መጠኑን እንዴት እንደሚታሰብ ለምሳሌ ሁሉም ዓይነት ታክስ በሚመለከተው በቤት አውቶሞቢል ተሽከርካሪ በምሳሌነት እንመልከት፡፡

 

የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋው ብር 400,000 የሲሊንደር አቅሙ 1300 የሆነ አዲስ አውቶሞቢል ወደ ሀገር ሲገባ:-

  • በቅድሚያ የጉምሩክ ቀረጥ የሚሰላ ሲሆን ማስከፈያ ዋጋው በጉምሩክ ቀረጥ ምጣኔ በማባዛት የሚሰላ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ተከፋዩ የጉምሩክ ቀረጥ 400,000 X 30%(ከፍተኛው መጣኔ) = 120,000  ይሆናል፡፡

  •  

    ቀጥሎ ኤክሳይዝ ታክስ የሚሰላ ሲሆን ስሌቱ የአውቶሞቢሉ የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ እና ተከፋዩ የጉምሩክ ቀረጥ በመደመር በኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ ማባዛት ነው፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ተከፋዩ ኤክሳይስ ታክስ መጠን (400,000 + 120,000) 5%= 26,000 ብር ይሆናል፡፡
  •  

    በሶስተኛ ደረጃ የሚሰላው ተከፋይ የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ሲሆን በዚህ ስሌት የአውቶሞቢሉን የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ፣ ተከፋይ የጉምሩክ ቀረጥ እና ኤክሳይዝ ታክስን በመደመር በተጨማሪ ዕሴት ታክስ መጣኔ  ይባዛል፡፡ በዚህ መሰረት የሚከፈለው ተጨማሪ ዕሴት ታክስ (400,000 + 120,000 + 26,000) 15% = 81,900 ብር ይሆናል፡፡
  •  

    በአራተኛ ደረጃ የሚሰላው ሱር ታክስ ሲሆን ስሌቱ የአውቶሞቢሉን የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ፣ ተከፋይ የጉምሩክ ቀረጥ፣ ኤክሳይዝ ታክስ እና ተጨማሪ እሴት ታክስ በመደመር በሱር ታክስ መጣኔማባዛት ነው፡፡ በዚህ መሰረት የሚከፈለው ሱር ታክስ (400,000 + 120,000 + 26,000 +81,900)10%= 86,190 ብር ይሆናል፡፡
  •  

    ተሽከራካሪው በመደበኛ አስመጪ(ከአምራች ድርጅት ውጪ…) የሚመጣ ከሆነ በአምስተኛ ደረጃ ተከፋዩን ዊዝሆልዲንግ ታክስ ነው፡፡ ይህ ታክስ የሚሰላው የቀረጥ ማስከፈያ ዋጋን በዊዝሆልዲንግ ታክስ መጣኔ በማባዛት ነው፡፡ በዚህ መሰረት ተከፋዩ የዊዝሆልዲንግ ታክስ 400,000 X 3%= 12,000 ብር ይሆናል፡፡
  •  

በመጨረሻም የስሌት ደረጃ ሁሉም ተከፋይ ቀረጥና ታክስ የሚደመሩ ሲሆን በዚህ መሰረት መንግስት ከዚህ አውቶሞቢል የሚሰበስበው ቀረጥና ታክስ ስሌት

120,000 + 26,000 + 81,900 + 86,190 + 12,000= 326,090 ብር ይሆናል፡፡

 

ማሳሰቢያ፡- ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የአገልግሎት ጊዜያቸው መሠረት በማድረግ የተለያየ ኤክሳይዝ ታክስ ይጣልባቸዋል፡፡

.

በብዛት የተነበቡ ዜናዎች

  • "ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ህግን በማክበርና የልዕቀት ማዕከል በመሆን አርአያ ሊሆኑ ይገባል" የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው Fri, 29 Oct 2021
"ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ህግን በማክበርና የልዕቀት ማዕከል በመሆን አርአያ ሊሆኑ ይገባል" የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው
  • "የሀገራችንን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም በሚደረገው ጥረት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሳናሸልብ ተግተን እንሰራለን " ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ (የገቢዎች ሚኒስትር) Wed, 4 Jan 2023
"የሀገራችንን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም በሚደረገው ጥረት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሳናሸልብ ተግተን እንሰራለን " ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ (የገቢዎች ሚኒስትር)