Asset Publisher

null የታክስ መረጃ አስተዳደርን ለማዘመ እየተሰራ ነው

የገቢዎች ሚኒስቴር የገቢ አሰባሰቡን በቴክኖሎጂ ማዘመን እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ መረጃ አስተዳደር ሥርዓት የ2014/2015 በጀት ዓመት አፈፃፀም ብቃት ያለው እና ውጤታማ መሆኑን በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲትን ከፌዴራል ዋና ኦዲተርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት፣ በተገኘው ኦዲት መሠረት የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ መረጃ አስተዳደር ሥርዓቱን ለማሻሻል መርሃ ግብር አዘጋጅቶ እየወሰደ ያለውን አዎንታዊ እርምጃ በማድነቅ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የገቢ አሰባሰቡን በቴክኖሎጂ አዘምኖ ቢሰራ አገሪቱ በምታመነጨው ኢኮኖሚ ልክ ገቢ መሰብሰብ እንዲሚያግዘው አስገንዝበዋል፡፡

የተከበሩ ወይዘሮ አራሬ አክለውም የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበርንና ሐሰተኛ ደረሰኝን በማስቀረት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ በመሰብሰብ አገሪቱን ከእርዳታና ብድር እንድትላቀቅ የገቢዎች ሚኒስቴር በትኩረት መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

አገሪቱ ከምታመነጨው ገቢ የሚገባትን ያህል ገቢ መሰብሰብ እንድትችልም የገቢዎች ሚኒስቴር በኦዲት ግኝቱ ከተሰጠው አስተያየት በተጨማሪ ሰፋ አድርጎ በማየት መሥራት እንደሚገባ አሳስበው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በመሥራት የታክስ አጭበርበርንና ሐሰተኛ ደረሰኝን መከላከል እንደሚቻልም የተከበሩ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢዋ አያይዘውም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በአዋጅ ብቻ መተግበር ስለሚያስቸግረው የአፈጻጸም መመሪያዎችን አውጥቶ ቢሠራ ለታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ሥራው ስለሚጠቅመው በኦዲት ግኝቱ መመሪያ ማውጣት አለበት ተብሎ የተሰጠውን አስተያየት መፈተሽ እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው የክዋኔ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ሱመያ ደሳለው በበኩላቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር እንዲሁም ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር ተባብሮ ቢሰራ የታክስ ማጭበርበርንና ሐሰተኛ ደረሰኝን በመካለከል የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ስለሚረዳው ከሌሎች አካላት ጋር ለመገናኘት የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ማዘመን እንዳለበበት ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሶፍትዌሮችን አበልፅጎ መሥራት ቢችል የታክስ ማጭበርበርንና ሐሰተኛ ደረሰኝን በመከላከል አገሪቱ ከምታመነጨው ገቢ የተሻለ ግብር መሰብሰብ የሚያስችለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በአዋጅ ቁጥር 983/2005 በአንቀጽ 136 ንዑስ አንቀጽ 2 መመሪያ እንደሚያወጣ በተደነገገው መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የአፈጻጸም መመሪያ አውጥቶ ቢሠራ ለታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ስለሚረዳው በኦዲት ግኝቱ በተሰጠው አስተያየት መሠረት የአፈጻጸም መመሪያዎችን አውጥቶ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎችን በቴክኖሎጂ አዘምኖ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ ቢሠራ የታክስ ማጭበርበርንና ሐሰተኛ ደረሰኝን መከላከል ስለሚችል የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ የሚረዳው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው ቀደም ብለው የገቡት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች በነበረው መሠረተ ልማት አለመስፋፋት ቴክኖሎጂ ያልተገጠመላቸው ስለነበሩ ከሌሎች ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቻቸውና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቴክኖሎጂ አጋዥነት ተቀናጅተው ለመሥራት ሲቸገሩ እንደነበር ጠቁመው፤ በቅርብ የገቡት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ግን በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማድረግ የታክስ መረጃ አስተዳደርን ለማዘመን በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ባለሙያዎችን መድበው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰጠው አስተያየት መሠረት መመሪያዎችን ለማውጣት በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የገቢዎች ሚኒስቴር ገቢ ለመሰብሰብ ባቀደው ልክ እየሠራ ቢሆንም ቋሚ ኮሚቴውና የፌዴራል ዋና ኦዲተር የሰጣቸውን አስተያየቶች በመውስድ አገሪቱ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ስለሚረዳ አስተያየቱን በአዎንታ መቀበላቸውን ተናግረዋል፡፡

ምንጭ:- ፓርለማ

Most Viewed Assets

በብዛት የተነበቡ ዜናዎች

  • "ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ህግን በማክበርና የልዕቀት ማዕከል በመሆን አርአያ ሊሆኑ ይገባል" የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው Fri, 29 Oct 2021
"ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ህግን በማክበርና የልዕቀት ማዕከል በመሆን አርአያ ሊሆኑ ይገባል" የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው
  • "የሀገራችንን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም በሚደረገው ጥረት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሳናሸልብ ተግተን እንሰራለን " ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ (የገቢዎች ሚኒስትር) Wed, 4 Jan 2023
"የሀገራችንን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም በሚደረገው ጥረት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሳናሸልብ ተግተን እንሰራለን " ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ (የገቢዎች ሚኒስትር)